የኢትዮጵያ የጥንት ጸሐፊዎች ታሪክን ከሃይማኖት ጋር አያይዘው በማቅረብ ተግባር በጣም የታወቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ከሀገራችን ታሪክ ጋር በቅርብ ያዛምዱታል፡፡ ሕዝቡ ሳይቀር ከጥንት እስራኤል አገር የመጣ ነው እያሉ ይተርታሉ፡፡ የንግሥት ሳባ እና ቀዳማዊ ምኒልክ “ታሪክ” ይህን ነው የሚያስተምረው፡፡ ካህናቱ እንደ እውነት አድርገው ተቀብለውታል፡፡ በየመድረኩም ይሰብኩታል፡፡ በካህናት አንደበት የሚነገር ደግሞ እንደ ሃይማኖት አጥብቆ ስለሚያዝ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ትውፊትና አፈ ታሪክ ውስጥ በጣም ዘልቆ ገብቷል፡፡ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ ካህናቱና ተራው ህዝብ እንኳ ሳይቀር፣ ዘር ሲቆጥር ወይም ከንግሥት ሳባና ከልጇ ከቀዳማዊ ምኒልክ፣ ወይም ከምኒልክ ጋር የእስራኤል ታቦት ሰርቀው መጡ ከሚባሉት ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እሥራኤል ካንደኛው ነው የሚጀምሩት፡፡ ሰለሞናዊ የሚባለው ሥርወ መንግሥት መነሻው ከዚሁ ተረት ነው፡፡ የፈላሻ ሕዝብም እንደዚሁ፡፡
ይህ ከየብራና መጻሕፍቱ ሲገለባበጥ፣ በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻና በሃያኛው መጀመሪያ ላይ እስከተነሱት የታሪክ ጸሐፊዎቻችን ድረስ ደርሷል፡፡ በተለይ አለቃ ታዬ የጻፉት የኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ ነገር እጅግ ተበክሏል፡፡ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእሥራኤል ወይም ከከነዓን እንደመጣ አድርገው ነው የጻፉት፡፡ ይህ ነገር አሁን እኛ ለምናደርገው የታሪክ ምርምር አንዳንድ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ቃለ መጠይቅ የምናቀርብላቸው አዛውንት በዚህ ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የታተመውን የአለቃ ታዬ መጽሐፍ ያነበቡ ናቸው፡፡ ታዲያ እንደ ሕዝባቸው ታሪክ አድርገው መልሰው የሚነግሩን ከአለቃ ታዬ ያገኙትን ይሆንብናል፡፡
ሌላው የታሪክ ፀሐፊ አቶ አጽመ ጊዮርጊስ ግን፣ ስለ ንግሥት ሳባ እና ቀዳማዊ ምኒልክ ተረት የተለየ አስተያየት አላቸው፡፡ ከቀድሞ ጀምሮ የሚነገረውን ይመዘግቡና ሲጨርሱ እንዲህ ሲሉ በፈገግታ ይደመድሙታል፡፡ “ይህ ነገር እንቅፋት፣ ጥፋት ነው – እውነቱ ከዉሸት ስለአልተለየ፡፡ በዘንዶ መቅደስ ጽላተ ሙሴ ገባችበት፡፡” ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከእሥራኤል ጋር የማያያዝ ነገር ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃ የለውም፡፡ እንዲያውም ያሉን አስተማማኝ የታሪክ ቅሪቶች በቀጥታ ይቃወሙታል፡፡ቀዳማዊ ምኒልክና ጓደኞቹ የእሥራኤል ወጣቶች ከኢየሩሳሌም ታቦት ሰርቀው አክሱም ከተማ ቤተ መቅደስ አኖሩት በሚባልበት ጊዜ አክሱም ገና አልተቆረቆረችም፡፡ አክሱም ከተማና የታሪክ ዘመን የሚጀምረው የቀዳማዊ ምኒልክ አባት ነው ከሚባለው ከንጉሥ ሰለሞን 800 ዓመታት ያህል ቆይቶ ነው፡፡ የአይሁዶችም ሃይማኖት በዚያን ጊዜ ተመሥርቶ፣ የንጉሡ፣ የተከታዮቹና የሕዝቡ ሁሉ ቋንቋ ወደ ግዕዝ ተተርጉሞ ነበር የሚባለውም እንዲያው የሃይማኖት ነው እንጂ የታሪክ መሠረት የለውም፡፡ ግዕዝ የመጻፍያ ቋንቋ የሆነው ከሰለሞን በኋላ 1150 ዓመታት ያህል ቆይቶ መሆኑ በሚገባ ተረጋግጧል፡፡ የአክሱምም ሆነ የቅድመ አክሱም ነገሥታት፣ የክርስትና ሃይማኖት በ350 ዓም አካባቢ ከመመሥረቱ በፊት የነበሩት በሙሉ በአምልኮ ጣዖት ይኖሩ ነበር እንጂ የአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮች እንዳልነበሩ በሚገባ ታውቋል፡፡ በተለይ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ነው አቶ አጽሜ በኢትዮጵያ ያለውን ሃይማኖት “በኦሪት ቅመም የተቀመመ፣ በአረመኔ ቅቤ የጣፈጠ ክርስትና ነው” ብለው በረቀቀ አንደበት ሂስ ያቀረቡት፡፡ መቸ እንደጀመረ ቁርጥ ያለ መረጃ ገና የለንም፡፡ ግን ከአክሱም ዘመነ መንግሥት የመጡልን አስተማማኝ ሰነዶች አይጠቅሱትም፡፡ ይህም በዚያን ዘመን ገና እንዳልተፈጠረ ያመለክታል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ሐሳቡ ከኢትዮጵያ ጋራ ተያይዞ የምናገኘው በ850 ዓም አካባቢ በአንድ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ ነው፤ ማለትም የአክሱም መንግሥት ከወደቀ በኋላ ‹የጨለማ ዘመን› ተብሎ በሚጠራው ዘመን፡፡ ይህም መሆኑ አያስደንቅም፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ያሉ ተረቶች የሚያብቡት ተጨባጭ የታሪክ መረጃ በማይገኝበት ‹የጨለማ ዘመን› ነው፡፡ በሀገር ውስጥ የመንግሥት ኃይል ወድቆ፣ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ተዳክሞ የትምህርት ተቋሞች ተበታትነው፣ የታሪክ ቅርስ ለማቆየት በማይቻልበት ጊዜ ነው በተለይ አፈ ታሪክ የሚስፋፋው፡፡ ከዓመታት በኋላ በጽሑፍ ይሰፍርና ይተላለፋል፤ ሥር ይሰድዳል፡፡ የንግሥተ ሳባና የቀዳማዊ ምኒልክ [ታሪክ] መልክ ይዞ በመጽሐፍነት ተቀናብሮ ክብረነገሥት በሚል አርዕስት የተጻፈው በአጼ ዓምደ ጽዮን ዘመን (እ.ኤ.አ. ከ1313 – 1344) መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የአጻጻፉም ዋና ሂደት በአደፋ/ላሊበላ መንግሥትና በኋላ ‘ሰለሞናዊ ነኝ’ ብሎ በሚነግሠው አዲስ ሥርወ መንግሥት መካከል ከነበረው የሥልጣን ትግል ጋር የተያያዘ መሆኑን ብዙ ነጥቦች ያመለክቱናል፡፡ የሰለሞናውያን ንግሥና ከተቋቋመ በኋላ፣ የሕገ መንግሥትነት ባሕርይ አግኝቶ አጼ ኃይለ ሥላሴ (ከ1923 – 1966) ከሥልጣን እስኪወርዱ ድረስ ይቆያል፡፡
ሌሎችም በተመሳሳይ ዓይነት የተፈጠሩ ተረቶች በታሪካችን ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ ያላቸው ሞልተዋል፡፡ የፈላሾች ጥንታዊ አይሁድነት ጉዳይ አንደኛው ነው፡፡ በየመጽሐፉ ጉዲት እየተባለች የምትጠራዋ ሴትም በሚነገርላት ታሪክ አንፃር እንዲያው የተረት ፈጠራ ናት፡፡ በዚያው ‹የጨለማ ዘመን› በተባለው ጊዜ ነው የተፈጠረችው፡፡ የአክሱምን ትልቅ ኃይል አወዳደቅ በተጨባጭ ታሪክ ማስረዳት ሲያውክ፣ አንድ የታወቀች ሴት ከሌላ ዘመን፣ ከሌላ ሕዝብ፣ ከሌላ አካባቢ ተወስዳ በአክሱም ታሪክ ላይ የተወረወረች ጎበዝ መሪ ናት፡፡
ስለእነዚህ ትረታዎች ይዘት መሠረታዊ ችግር ትክክለኛውን መስመር የሚያመለክቱ አንዳንድ የታሪክ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ነገር ግን፣ የእምነት ኃይል ጠንካራ ስለሆነ ስለ ቀዳማዊ ምኒልክ አክሱማዊነት የዘውድ ሥርዓት ደጋፊ ከሆኑ ግለሰቦች ጀምሮ እስከ ተራ ቤተሰቦች ድረስ ይነገራል፡፡ ካህኑም ይተርተዋል፡፡ በገና ደርዳሪውም ሥነ ጥበቡ ከዚያ የተገኘ ነው እያለ ያወሳናል፡፡ የጉዲትም ተረት መነገር ቀጥሏል፡፡
እዚህ ላይ ማንሳት የተፈለገው ዋና ነጥብ፣ ከአባቶች የሚነገሩን አፈ ታሪኮች ሁሉ እንዳሉ እንደ ታሪክ መወሰድ እንደሌለባቸው፣ በታሪክ ምርምር ዘዴ አስተማማኝነታቸው መለካት እንደሚችልና ትክክለኛ ሥፍራቸውን ማግኘት እንደሚገባቸው ነው፡፡ ይልቁንም አሁን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት ሥርዓት በተዘረጋበት ጊዜ የየብሔረሰቡ ምሁራን የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ያልተጣሩ ተረቶችና አፈ ታሪኮች ይዞ መሯሯጥ ለሕዝቡ የዘለቄታ ታሪክ ይዘት ጥፋት እንደሚያመጣ መገንዘብ ያሻል፡፡
ይህ ጽሑፍ ‘ውይይት’ በሚሰኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ማኅበር መጽሔት፣ ቅጽ 1፣ ቁጥር 2፣ 1984 የታተመ ነው። ወደዚህ ጽሑፍ ስለጠቆሙን አቶ ሙሉጌታ ወልደጻዲቅ በጣም እናመሰግናለን።
- US says Ethiopian, Eritrean, and Amhara forces committed ‘crimes against humanity’ in the Tigray war - 20th March 2023
- የኢትዮጵያን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከእሥራኤል ጋር ማያያዝ ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃ የለውም:ፕ/ር ታደሰ ታምራት - 12th February 2023
- Dozens of civilians killed, property burned by Amhara forces in Oromia zone - 26th January 2023